• May 20, 2024

4-3-3 ስፖርት በኢትዮጵያ

ከእሁድ እስከ እሁድ ፈጣን የመረጃ ምንጭ!

የብሄራዊ ቡድናችን የአሜሪካ ጉዞና አጠራጣሪው የወዳጅነት ጨዋታ….

ByLeo Simera

Jun 8, 2023

የብሄራዊ ቡድናችን የአሜሪካ ጉዞና አጠራጣሪው የወዳጅነት ጨዋታ….

➡️ የጉዞው ዓላማ ምንድነው? ⚽ ዋሊያው ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ምድር ለመጫወት፥ የጉያና ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ ሀገር ጋር ለመጋጠምና በወዳጅነት ጨዋታ ለመፈታተሽ ቀጠሮ ይዘዋል

➡️ መቼና የት? ⚽ ሀምሌ 1/2015 ወይም july 8/2023 በፔንሴልቪንያ ግዛት ቸስተር ፊላዴልፊያ በሚገኘው subaru park ስታዲየም ጨዋታውን ለማካሄድ ቀን ተቆርጧል፤ ስታዲየሙ 18ሺህ 500 ተመልካች የመያዝ አቅም አለው

➡️ ስለ ዋሊያው ተጋጣሚ ጉያና ⚽ ጉያና በደቡብ አሜሪካ አህጉር የምትገኝ በሰሜን በኩል በአትላንቲክ ውቂያኖስ፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ በብራዚል፣ በምዕራብ በቬኑዚዌላ እንዲሁም በምስራቅ በስሪናም የተከበበች 800ሺህ ህዝብ ያላት ሀገር ነች፤ ጉያና ማለት “የብዙሀን ውሃ ምድር” የሚል ትርጉም አለው ሀገሪቷ በደቡብ አሜሪካ ብትገኝም የእግርኳስ ተሳትፎዋ ግን በሌላ አህጉር ነው፤ የሰሜን አሜሪካና ካሪቢያን ሀገራት የእግርኳስ ማህበር አባል ነች፤ ብሄራዊ ቡድኗ “ወርቃማው ጃጉዋር” የሚል ቅፅል ስም አለው፤ በ2019 በኮንካፍ ጎልደን ካፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ ነበር፤ አሁንም ማጣሪያ ላይ ይገኛል፤ በወቅቱ የፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 170ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ ዋሊያው ደግሞ 142ኛ ነው

➡️ ስለ አሰልጣኙና ተጫዋቾቹ ⚽ ዋና አሰልጣኙ ጀማል ሳባዝ ይባላሉ፤ የ59 አመት የትሪንዳድ ዜጋ ናቸው፤ ከተጫዋቾቹ መካከል በእንግሊዝ semi professional እና non league የሚጫወቱ ስምንት ተጫዋቾች አሏቸው፤ ዘጠኝ ያህሉ በሀገር ውስጥ ሊግ ይጫወታሉ፤ የብሄራዊ ቡድኑ የቅርብ ጨዋታ ከሞንትስራት ጋር ነበር፤ 0-0 ተለያይተዋል፤ ሰኔ 10 ደግሞ ከግሪናዳ ጋር በጎልድ ካፕ ማጣሪያ ይጫወታሉ፤ ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ጃማይካ በልምምድ ቆይተው በዚህ ሳምንት ወደ አሜሪካ ፍሎሪዳ ሄደዋል

➡️ ጨዋታውን ያዘጋጀው ማነው? ⚽ የዋሊያውንና የወርቃማ ጃጉዋርን ጨዋታ ያዘጋጀው ሲጂኤ ኒውማን ኮርትኒ የተባለ፥ ከ2009 ጀምሮ በፊፋ እውቅና ያለው፥ በአሜሪካ ተመዝግቦ የሚገኝና ዋና መቀመጫው ፍሎሪዳ የሆነ የጨዋታዎች ኤጀንት ነው፤ የተቋሙ ስም ዞንድ ይባላል፤ መስከረም ላይ የፖርቴሪኮና የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ጨዋታን አዘጋጅቶ ሳይካሄድ ቀርቷል፤ በአየር ፀባይ መለወጥ የሚል ምክንያት አቅርቧል፤ ከዚህ ሌላ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ያዘጋጀው ጨዋታ የለም፤ ይህ ሁለተኛው ነው፤ ለዚህ ጨዋታ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ውል ያሰረው ጥቅምት ላይ ነበር

➡️ አሜሪካ የሚሄደው የዋሊያው ልዑክ ስንት ነው?⚽ የልዑኩ ይፋዊ ቁጥር 30 ነው፤ ሀያ አምስቱ ተጫዋቾች ናቸው፤ ቀሪው የአሰልጣኝ ቡድን ይሆናል ተብሏል

➡️ ብሄራዊ ቡድናችን ምን ያገኛል? አዘጋጁስ? ⚽ ለ30 ሰው የጉዞ፣ የሆቴል፣ የልምምድ ሜዳ አቅርቦትና ሌሎች ወጪዎች በሙሉ በአዘጋጁ ይሸፈናል፤ ብሄራዊ ቡድናችን አሜሪካ ሲደርስ 5ሺህ ዶላር ያገኛል፤ የስታዲየሙ ሙሉ ገቢ ግን የአዘጋጁ ሲጂኤ ኒውማን ኮርትኒ ነው፤ ፌዴሬሽኑ ከ30 በላይ ልዑክ ይዞ የሚሄድ ከሆነ የቀሪዎቹን ወጪ ራሱ ይችላል

➡️ የቪዛ ጉዳይስ? ⚽ አስገራሚው መረጃ ይህ ነው፤ በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለቪዛ ቀጠሮ የሰጣቸው ለጨዋታው ከተያዘው እለት ከሁለት ቀን በኋላ ነው፤ ፌዴሬሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር በመተባበር ቀጠሮውን ለማሳጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል፤ የኤምባሲው ምላሽ እየተጠበቀ ነው

➡️ ቀኑና ቦታው ያስነሳው ቅሬታ ⚽ ጨዋታው የሚከናወንበት ቀን ሀምሌ 1 ወይም july 8 የሰሜን አሜሪካ የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል በቴክሳስ ዳላስ የሚጠናቀቅበት እለት ነው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዚህ ዝግጅት ላይ ይታደማል፤ የወዳጅነት ጨዋታውም በዚህ ቀን መሆኑ ቅሬታን ፈጥሯል፤ ጨዋታው የሚደረግበት ቦታ ፊላዴልፊያም ለምን እንደተመረጠ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ይኖራል፤ ከእነዚህ አካባቢዎች ፊላዴልፊያ ከሁለት ተኩል እስከ ሶስት ሰዓት የመኪና መንገድ ይፈጃል፤ ጨዋታው የሚካሄድበት ቀንና ቦታው ወጣ ማለቱ በብዙዎች አልተወደደም

➡️ ቀኑና ቦታውን ሊቀየር ይችላል?⚽ የስፖርት አፍቃሪውን ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ አመራሮች አቅርቤ ነበር፤ የጨዋታው ዋና አላማ ወዳጅነትና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም በአሜሪካ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በብዛት ለማግኘት በመሆኑ ብሄራዊ ቡድናችንም በሀገሩ ደጋፊ መታጀብ እንዳለበት ስለሚታመን የፌዴሬሽኑ አመራሮች ቅሬታውን መቀበላቸውን ለአዘጋጁም አማራጭ መፍትሄ ካለ በይፋዊ ደብዳቤ ማሳወቃቸውን ነግረውኛል፤ ከፌዴሬሽኑ ባገኘሁት መረጃ ቀንና ቦታው የመቀየር እድሉ ሰፊ ነው

➡️ ትኬቱ የት ይገኛል?⚽ ትኬቱ የሚሸጥበት ዌብሳይት ቀደም ብሎ ይፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ግን ዌብሳይቱ አይሰራም፤ ምክንያቱን ለማወቅ የዌብሳይቱን ባለቤት የፊላዴልፊያ ዩኒየን የትኬት ጉዳዮች ተወካይን አነጋግሬ ነበር፤ ትናንት ማምሻውን መልስ ሰጥተውኛል፤ “ጨዋታው ስለመካሄዱ ማረጋገጫ ስላላገኘንና ሊቀየር ስለሚችል ለጊዜው ትኬት መሸጥ አቁመናል፤ ይህን ጨዋታ ከመርሀ ግብሩ ውጪ አድርገነዋል” ብለውኛል

➡️ ማጠቃለያ⚽ የቪዛ ቀጠሮው ለጨዋታው ከተያዘው ሁለት ቀን በኋላ ነው፤ ለማሳጠር ጥረት እየተደረገ ቢሆንም መልስ አልተገኘም፤ ትኬት መሸጥም እንደቆመ ተረጋግጧል፤ ቦታውና ቀኑ እንዲለወጥ ግፊት ጨምሯል፤ የአዘጋጁ ምላሽ ይጠበቃል፤ በመሆኑም የዋሊያውና የወርቃማ ጃጉዋሮቹ የአሜሪካ የወዳጅነት ጨዋታ በተያዘለት ቀንና ቦታ የመካሄዱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፤ በሁለቱ ፌዴሬሽኖችም ሆነ በአዘጋጁ በኩል ግን ስለጨዋታው ቀን መቀየር ወይም መሰረዝ በይፋ የተገለፀ ማረጋገጫ የለም(ታምሩ ዓለሙ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *