• Fri. Nov 20th, 2026

የንጎሎ ካንተ ህይወት ታሪክ ክፍል አንድ

Byadmin

Oct 23, 2024

👉 1 ሜትር ከ68 ሴንትሜት ብቻ ቁመት ያለው ሜዳ ከገባ ጨዋታ እስኪጠናቀቅ በሙሉ አቅሙ ሲሮጥ ፣ኳስ ሲቀማ እና ሲቀበል የሚታይ ታታሪ ንጉሎ ካንተ ብቃቱ በተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት ከብዙ ጨዋታዎች ርቆ ከቆየ በኋላ ምስጋና ለአዲሱ አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል ይሁንና ንጉሎ ካንተ እንደገና ምርጥ ብቃቱ እንድናይ ችለናል። በዚህ የውድድር አመት በቻምፒየንስ ሊግ በነበሩ ጨዋታዎች በተደጋጋሚ የጨዋታ ኮኮብ ተብሎ መመረጥ ችለዋል።

👉 የንጎሎ ካንተ ወላጆች በ1980 ከአፍሪካዊት ሀገር ማሊ ኑራቸው ለመሻሻል እና የተሻለ ኑሮ ለመኖር በማሰብ ወደ ሀገር ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ተሰደዱ። እ.አ.አ መጋቢት 29 1991 ንጎሎ ካንተ በፓሪስ ተወለደ። ንጎሎ ካንተ የቤቱ የመጀመርያው ልጅ ሲሆን ከካንተ በመቀጠል 3 እህት እና ወንድሞችም ማለትም 2 ወንድሞች 1 እህት ማግኘት ችለዋል።አባቱ ገና ህፃን ሳለ ከዚህ አለም የተለየው ሲሆን ሌላ ታናሽ ወንድሙም በተጨማሪ በ2018 በልብ ድካም እንደሞተ የትናንቱ ትውስታ ነው። በዛም ሆነ በዚህ ህፃናት ማሳደግ እና የቤት ኑሮ መምራትም ወደ እናቱ መውደቁን ያስተዋለው ንጎሎ ካንተ የእናቱ ሸክም ለማቅለል በህፃንነቱ ወደ ቆሻሻ የሚጠራቀምበት ቦታዎች በመሄድ እንደገና ሊሰሩ የሚችሉ እቃዎች እየሰበሰበ በትንሽ ሳንቲሞች በመሸጥ እናቱን ማገዝ ተያይዘው።

👉 ግዜው 1998 ነበር ሀገረ ፈረንሳይ የአለም ዋንጫ አስተናግዳ ድል የተጎናፃፈች አመት ነው ለዚህ ጨዋታ ለመከታተል በመጡ የተለያዩ የአለማችን ሰዎች ምክንያት ንጉሎ ካንተ የተሻለ ገቢ ማግኘት ጀመረ። የሚውልበት በተለያዩ ትናንሽ የእግርኳስ ሜዳዎች እና ታላላቅ ሆቴሎች በሚገኙበት አከባቢ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የነበረው ካንተ ሳይገባው የእግርኳስ ፍቅር ወደ ውስጡ እየገባ መጣ። በዛን ግዜ ብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች የነበሩ በተለያዩ ምክንያት የሀገረ ፈረንሳይ ዜግነት ያገኙ ለፈረንሳይ የእግርኳስ ብሔራዊ ቡድን የወከሉ እንደነ ዜነዲን ዚዳን ፣ ቴሪ ሄኔሪ ፣ አኔልካ እና ሌሎች ተጨዋቾች ለዚህች አውሮፓዊት ሀገር ፈረንሳይ የአለም ዋንጫ ባለድል እንድትሆን በማድረጋቸው እንደነ ካንተ የመሳሳሉ ስደተኞች የእግርኳስ የተስፋ በር ከፈቱላቸው። ከአለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ ፈረንሳይ በእግርኳስ የነበራት እይታ ተቀይረዋል። በየቦታው የእግርኳስ አካዳሚ እንዲከፈት የተደረገ ሲሆን ንጎሎ ካንተም የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን ቻለ። ንጎሎ ካንተ እነዚህ እድሎችን ከተመቻቸለት በኋላ ከቤቱ የ15 ደቂቃዎች ጉዞ አድርገህ የምትገኘው #ሱረስነስ የእግርኳስ ክለብ እ.አ.አ በ2001 የእግርኳስ ህይወቱ ሀ ብሎ ጀመረ። ይህ የ10 አመት እያለ የጀመረው የእግርኳስ ጉዞ ብዙ ፈተናዎች እና ችግሮች ሲፈተኑት ታይተው ነበር።

👉 የሱረስነስ ሜዳዎች በዚህ ግዜ በአርተፊሻል ሳር ሙሉ ለሙሉ ተሰርቶ ቢገኙም ንጎሎ ካንተ በነበረበት ግዜ ግን ሁሉም ሜዳዎች ቀይ አፈር እንደነበረ ንጎሎ ካንተ ይናገራል። የመጀመሪያው የንጎሎ ካንተ አሰልጣኝ #ኦጂጅያ ስለ ካንተ እንዲህ ይላል። 🗣 “ስርአት ያለው ፈገግታ የማይለይበት ነበር። በነበረበት አጭር ቁመት እና ቀጫጫ አካላዊ መጠን ከንጎሎ ካንተ በፊት እንደሆኑት ተጨዋቾች እንደሚሆን ጠብቄ ነበር። ነገር ግን በመጀመሪያ የልምምድ ቀን ከእሱ በቁመትም በአካላዊ ግዝፈትም ከእሱ የሚበልጡ ኳስ እየቀማ ሳየው ግን በጣም ተገረምኩ። ከሁሉም ነገር የሳበኝ ግን እንደ ሌላ ልጅ ኳስ ቀምቶ ዝም ብሎ የሚይዝ ሳይሆን በቶሎ ለቡድን አጋሮቹ የሚሰጥ ራስ ወዳድ ያልሆነ ተጨዋች መሆኑን ነበር።”

👉 በተጫወተበት የእድሜ ክልል ለእኩየቹ ይሁን ከእሱ በእድሜ ለሚበልጡ ኳስ ሲጫወት ይበልጣቸው ነበር ሲል ታሪክ ካንተ ይናገራል። ከአመት አመት ደረጃ ከፍ እያለ የታየው ካንተ የ17 አመት በሆነበት ግዜ ከ20 አመት በታች ክለብ መጫወት የጀመረ ሲሆን በፈረንሳይኛ “ፒቲቲ ፓውስ” ማለትም “ትንሹ ታላቅ” የሚል ስም አወጡለት። ይህ በጣም ቀጫጫ ከመሆኑ የተነሳው ለእሱ የሚሆን ማልያ ማግኘት ሲቸገር የነበረው ካንተ የድሮ ስእሎችን ስታይ በጣም ነው የሚያስገርመው። ከቡድን አጋሮችም ይሁን ከአሰልጣኞቹ በጣም ምርጥ ግንኙነት የነበረው ካንተ በእግርኳስ ከነበረው ህይወት ውጪ ስለ ቤተሰቡ እና ስለ አኗኗሩ የሚያውቅም አንድም ሰው አልነበረም። በካንተ እድገት የማይናቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የሱረስነስ ክለብ ፀሓፊ #ፐር_ቪላ እንዲህ ይላል 🗣 “የካንተ ወላጅ እነማን እንደሆኑ እንዴት እንደሆኑ የማስታውሰው ነገር የለም። በዚያን ግዜ የነበሩ ህፃናት ተጨዋቾች ቤተሰባቸው የምንጠይቀው የሆነ ችግር ሲያጋጥማቸው አልያም መጥፎ ባህሪ የሚያሳዩ ተጨዋቾች ሲኖሩ ብቻ ነው። ያ ግን ንጎሎ ካንተ አልነበረውም ሁሌ ችግር ሲያጋጥመው ለሰው አይናገርም በእሱ ፈንታ በፈገግታ ሁሉም ነገር ያልፈዋል በተጨማሪም ካንተ ስነ ስርዓት ያለው ተጨዋች ስለነበረ ወላጆቹ ለመጎብኘት ምንም እድል አላገኘንም።” ሲል ስለ ካንተ ይገልፃል። ለምሳሌም ካንተ አባቱ በሞተበት ግዜ ማንም ተጨዋች ይሁን የቡድን አጋሮች የሚያውቅ እንዳልነበረ የሱረስነስ ፀሐፊ የነበረው ይናገራል።

👉 የሚገርመው ግን ካንተ በእያንዳንዱ ጨዋታ ምርጥ ብቃቱ ማሳየት ቢችልም የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ግን አይናቸው ሊጥሉበት አልቻሉም። ቪለ ለዚህ ተስፋ ያለው ታታሪ ተጨዋች ይዞ በልምምድ እና የፈተና ቦታዎች ሲንቀሳቀስ በነበረበት ግዜ እንደነ ሬንስ፣ ሎረንቴ፣ ፒኤስጂ የመሳሰሉት የፈረንሳይ ክለቦች ዋና መስፍርታቸው ቁመት ያላቸው ተጨዋቾች በመሆኑ ካንተ የነበረው ምርጥ ብቃት እና ታታሪነት ማስተዋል እንዳይችሉ አደረጋቸው። “በአንድ የመምረጫ ጨዋታ በነበረበት ግዜ ካንተ በሁለት ሴንት ሜትር የሚበልጠው ጫማ አድርጎ ዝናብ በሚዘንብበት ሰአት በጭቃ የተሞላው ሜዳ ላይ ሲጫወት አስታውሳለሁ” ያለው ቪለ “በዚያ ጨዋታ በጣም ቀጫጫው ተጨዋች ካንተ የነበረ ሲሆን በቁመትም ከቡድን አጋሮቹ በጣም ያነሰ ነበር። ነገር ግን ከማንም ተጨዋች በላይ በጨዋታ የበላይነት ወስዶ በማጠናቀቅ አስገራሚ የሆነው ብቃቱም አሳይቶናል። ነገር ግን በዚያን ግዜ ካንተ ወደ ታላቅ ክለብ የሚሄድበት እድል ሳይሳካ ቀረ። ያ ታታሪው፣ አይደክሜው ንጎሎ ካንተ በዚያ ሰአት ምንም እንኳን ባይመረጥም ከተመረጡ ቡድን አጋሮቹ በመሆን በጣም ደስታ የተሞላው፣ በፈገግታ ከቡድን አጋሮቹ ፎቶ ሲነሳ ሳይ ግን ከማንም ተጨዋች በላይ የተሳካለት ተጨዋች እንዲሆን እና በአለም ታላላቅ ሊጎች እንዳየው ምኞቴ በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ” ሲል ቪለ ደስ የሚል ትውስታ ይናገራል።

👉 ሁል ግዜ ጥረቱ የማያቆም ጥቁሩ ፈርጥ ንጎሎ ካንተ በሱረስነስ በቆየበት 10 አመታት በጣም ተወዳጅ ፣ ሁሉም የቡድን አባል የሚሳሱለት፣ ታታሪ፣ በፈገግታ የተሞላ እና ጠንካራ እንደነበረ የንጎሎ ካንተ ታሪክ ይናገራሉ። ግዜው እ.አ.አ 2009/10 በ9ኛው ዲቪዝዮን ሲጫወት የነበረው ክለብ ሱረስነስ 19 ጨዋታዎች አድርጎ 10 ጎል በማስቆጠር ኳስ በተደጋጋሚ ከመንጠቅ በተጨማሪ ብዙ ጎሎች ማስቆጠርም አክሎበት ነበር። ይሁን እንጂ እድሜው 19 ደርሶ ስለነበር ምንም አይነት የፕሮፌሽናል ፊርማ ሳይኖረው አለም ሳታውቀው በመቆየቱ ትልቅ ደረጃ ሳይደረስ በለጋ እድሜው በከንቱ እንዳይቀር የካንተ አሰልጣኞች ስጋት አድሮባቸው ነበር።
.
.
.
ይቀጥላል…

✍️|| @atsbaha12

By admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *