ግብጻዊው ኢንተርናሽናል አጥቂ ሞሀመድ ሳላህ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ብራይተን ሆቭ አልቢየንን አስተናግዶ ከመመራት ተነስቶ ሁለት ለአንድ ባሸነፈበት ግጥሚያ ላይ የማሸነፊያዋን ጎል በማስቆጠር ለአንድ ሳምንት ያህል በፔፕ ጋርዲዮላው ማንቺስተር ሲቲ ተወስዶበት የነበረውን የሊጉን መሪነት በድጋሚ ቡድኑ እንዲረከብ ማድረግ ችሏል።
አጥቂው ሞሀመድ ሳላህ ተከላካዮቹ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ እና ቨርጅል ቫንዳይክ በቅርብ አመታት በነበሩ የቡድኑ ስኬቶች ውስጥ የነበራቸው ሚና እጅግ የላቀ የሚባል ነው።
አዲሱ የውድድር ዘመን ከተጀመረ አስር ሳምንታትን ያስቆጠረ ሲሆን ሶስቱም ተጫዋቾች ግን እስካሁን ድረስ በክረምቱ የሚያልቀውን የኮንትራት ውል ቆይታቸውን ተከትሎ የውል ማራዘሚያ ፊርማቸውን አላኖሩም።
ሳላህ ከቅዳሜው ድል በኋላ በX ገጹ ” የሊጉ መሪ መሆናችን ክለቡ የሚገባው ቦታ ነው ። ከዚያ ያነሰ መሆን የለበትም።ሁሉም ቡድኖች ጨዋታዎችን ያሸንፋሉ ነገር ግን በስተመጨረሻ ሻምፒዮን የሚሆነው አንድ ቡድን ነው” ሲል ጽሁፉን አስፍሯል።
የቀድሞ የማንቺስተር ሲቲ ተከላካይ ሚካህ ሪቻርድስ ለቢቢሲ ማች ኦፍ ዘ ዴይ ሊቨርፑል ለግብጻዊው አጥቂ ቢያንስ ተጨማሪ ሁለት አመት የኮንትራት ውል ቆይታ ማራዘሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል።
ሳላህ ለቀዮቹ በ364 ጨዋታዎች 220 ጎሎችን ከመረብ ማገናኘት ችሏል። ግብጻዊው አሁን ላይ አምስተኛው የሊቨርፑል የምንግዜውም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ተጫዋች ሆኗል።
ሳላህ የመርሲሳይዱን ክለብ ከተቀላቀለ በኋላ በልዩነት የቡድኑ ወሳኝ እና ቁልፍ ተጫዋች ሆኖ ቆይቷል።በፕሪሚየር ሊጉ ከ1992-93 የውድድር ዘመን ጀምሮ በጎሎች እና አሲስቶች አጠቃላይ ተሳትፎ የሚበለጠው በሰባት ተጫዋቾች ብቻ ነው።
በድምሩ 238 ጎል እና አሲስቶች በሊጉ አሉት። በአምስት የተለያዩ የውድድር ዘመናት አስር እና ከዚያ በላይ ጎሎች እና አሲስቶችን በማድረግ ከዌይን ሩኒ ጋር ሪከርዱን በጣምራ ይዟል።
ዘንድሮ ይህን ሪከርድ መስበር የሚችልበትም ሰፊ እድልም አለው። ከወዲሁ በአስር ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ስድስት ጎሎች እና አምስት አሲስቶች አሉት።
ሊቨርፑሉ በአዲሱ ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኙ አርኔ ሽሎት ስር በሁሉም መድረክ ውድድሮች ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 13ቱን ማሸነፍ ችሏል።
አሁን ላይ ግን አሳሳቢው ነገር በውድድር ዘመኑ መጨረሻ የሚጠናቀቀው የሞሀመድ ሳላህን ጨምሮ አሌክሳንደር አርኖልድ እና ቫንጃይክ ቆይታ ጉዳይ ነው።
የሶስት ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ወርቅ ጫማ አሸናፊ ግብጻዊ አጥቂ አስፈላጊነት ሜዳ ገብቶ በተሰለፈባቸው እያንዳንዱ ጨዋታዎች ላይ በሚገባ ታይቷል።