የእግር ኳስ ህይወቱን ሀ ብሎ የጀመረው በአርጀንቲና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሚሳተፈው ለትውልድ ከተማው ክለብ አትሌቲኮ ሴንትራል ኮርዳቦ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በመጫወት ነው። የዲባላ ቅፅል ስሙ ላ ጆያ ወይም ኤል ፒቤ ዴ ላ ፔንሲዮን ነው ፤ ዲባላ በአርጀንቲና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየቱን ቀጠለበት ፤ በዚህም በ40 ጨዋታዎች 17 ጎሎችን በማስቆጠር በክለብ አዲስ ሪከርድ አስመዘገበ ፤ ከዚህም በመቀጠል 38 ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ሌላ አዲስ ታሪክን አፃፈ ፤ እንዲሁም በአንድ የውድድር ዓመት ሁለት ሀትሪኮችን መሰራት ቻለ ፤ ዲባላ በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጎል ያስቆጠረ ብቸኛው ተጫዋች ነው ፤ የጣሊያኑ ክለብ ፓሌርሞ አርጀንቲናዊውን ታዳጊ ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው በዚህም ከሚጫወትበት ክለብ ጋር ድርድር ማድረግ ጀመሩ ፤ ፓሌርሞም ከስንት ድርድሮች በኋላ አርጀንቲናዊው ኮከብ በሚያዚያ 29,2012 ተጫዋቹን ማስፈረማቸውን ይፋ አደረጉ ፤ የፓሌርሞ ቡድን ፕሬዝዳንት ማውሪዚዮ ዛምፓሪኒ ስለ ዲባላ ዝውውር እንዲህ በማለት ተናገሩ ” እኛ ፓውሎ ዲባላን አግኝተናል ፤ እሱ አዲሱ ሰርጂዮ አጉዌሮ ነው በማለት አሞካሹት ፤ ፓሌርሞ ዲባላን ለማስፈረም €8.64 ሚሊዮን ዩሮ ከፍለዋል ፤ ዲባላም በፓሌርሞ ቤት ለአራት አመት የሚያቆየውን ውል ፈረመ ፤ ፓሌርሞ ከ ላዚዮ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ፓውሎ ዲባላ በጣሊያን ሴሪኤ የመጀመሪያ ጨዋታውን አደረገ ፤ ዲባላም በጣሊያን ሴሪኤ የመጀመሪያ ጎሉን ያስቆጠረው ፓሌርሞ ሳምፕዶሪያን 2-0 ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ነው ። ዲባላ በፓሌርሞ ጥሩ ጊዜ ማሳለፉን ቀጠለበት ፤ በተለይ 2014/15 የውድድር ዓመት ለፓውሎ ዲባላ የተለየ አመት ነበር ፤ በመጀመሪያ ዙር ብቻ በሴሪኤው በ18 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን አስቆጠረ ፤ በተለይ በፓሌርሞ ከፍራንኮ ቫዝኩዌዝ ጋር ጥሩ ጥምረት ፈጠሩ በዛን የውድድር ዓመት አርጀንቲናዊው ኮከብ ዲባላ 13 ጎሎችን አስቆጠረ ፤ 10 አሲስቶችን አደረገ ፤ በዚህም የታላላቅ ክለቦችን ቀልብ ሳበ ፤ የእንግሊዝ እና የስፔን ክለቦች አርጀንቲናዊውን ኮከብ ዲባላን ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው በዚህም ተጫዋቹ ከበርካታ ታላላቅ ክለቦች ጋር ስሙ መያያዝ ጀመረ ።
ቢሆንም ክለቡ ፓሌርሞ ተጫዋቹን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አልነበሩም ፤ ቢሆንም የጣሊያኑ ክለብ ጁቬንቱስ በዝውውሩ ላይ ገፋበት የጁቬንትስ ሀላፊዎች በተጫዋቹ ላይ ከፍተኛ እምነት ስላደረባቸው ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ ከፓሌርሞ ጋር ድርድር ማድረግ ጀመሩ ፤ ይህም ድርድር ተሳክቶ ሰኔ 4,2015 ጁቬንትሶች አርጀንቲናዊውን ኮከብ ፓውሎ ዲባላን በ€32 ሚሊዮን ዩሮ እና ተጨማሪ 8ሚሊዮን ዩሮ ለፓሌርሞ በመክፈል ኮከብን የግላቸው አደረጉ ። ዲባላም በጁቬንትስ ቤት 21 ቁጥር ማሊያን ተሰጠው ይህ ቁጥር ከዚ በፊት የጁቬንትስ አማካይ አንድሪያ ፒርሎ የሚለብሰው ነበር ፤ ዲባላ ለጁቬንቱስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው በነሀሴ 8,2015 በጣሊያን ሱፐር ካፕ ላይ ከላዚዮ ጋር ነበር ፤ ዲባላም ጠንክሮ በመስራት ራሱን ማሻሻሉን ቀጠለበት ፤ በጊዜው በጁቬንትስ ታላላቅ ተጫዋቾች ስለነበሩ ዲባላ ቋሚ 11 ውስጥ ለመግባት ተቸገረ ፤ ቢሆንም ጁቬንቱስ ሻንጋይን 2-0 ባሸነፉበት የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ዲባላ በ73ተኛው ደቂቃ ጎል አስቆጠረ ይህም በጁቬንቱስ ማሊያ የመጀመሪያ ጎሉ ሆኖ ተመዘገበለት ፤ ከዚህ በኋላ ዲባላ ከክለብ ጋር እየተግባባ መጣ በዚህም በነሀሴ 30,2015 ጁቬንቱስ በሴሪኤው ሮማን 2-1 ሲያሸንፉ ዲባላ በሊጉ የመጀመሪያ ጎሉን አስቆጠረ ፤ በዚህ ሲዝን ዲባላ በ16 ጨዋታዎች ላይ 6 ጎሎች እና 2 አሲስቶችን አደረገ ፤ ይህም በሬሺዮ ሲሰራ በየ151 ደቂቃው ዲባላ ጎል ላይ ተሳትፎ ያደርጋል ማለት ነው ፤ ዲባላ በቱሪን ጥሩ ጊዜ ማሳለፉን ቀጠለበት አብዛኛውን ጨዋታ ከተቀያሪ ወንበር እየተነሳ ነው የሚያደርገው ፤ ከኮፓ ኢታሊያ ጁቬንቱስ የከተማ ተቀናቃኙን ቶሪኖን 4-0 ሲያሸንፉ ዲባላ የመጀመሪያ የኮፓ ኢታሊያ ጎሉን ለጁቬንቱስ አስቆጠረ ፤ በየካቲት 23,2016 በቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በሜዳቸው ከባየር ሙኒክ ጋር 2-2 ሲለያዩ ዲባላ የመጀመሪያ የቻምፒየንስ ሊግ ጎሉን አስቆጠረ ፤ ዲባላ በእግርኳስ ህይወቱ የመጀመሪያ ጉዳቱን አስተናገደ ፤ ጉዳቱም የጡንቻ ጉዳት ነበር ፤ ተጫዋቹ ለተወሰኑ ወራት ከሜዳ ራቀ ፤ ቢሆንም ዲባላ ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ እያገገመ መጣ ይህም ለክለብ መልካም ዜና ነው ፤ ነገር ግን ከጉዳቱ አገግሞ እንደተመለሰ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በድጋሚ ሌላ አዲስ ጉዳት አስተናገደ ፤ ጉዳቱ አስከፊ እንዳልሆነ ዶክተሮቹ ተናገሩ ለአንድ ወር ከሜዳ ከራቀ በኋላ በይበልጥ ራሱን በማሻሻል ወደ ሜዳ ተመለሰ ፤ እንዲሁም ጁቬንቱስ በቱሪን ላዚዮን 3-0 ሲያሸንፉ ዲባላ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ሶስት ነጥብ እንዲያገኙ ከፍተኛ ሚና ተወቷል ፤ ዲባላ በሁሉም ውድድሮች ባደረገው 31 ጨዋታዎች ላይ 16 ጎሎችን አስቆጥሯል ፤ እንዲሁም በውድድር ዓመቱ በሁሉም ውድድሮች 23 ጎሎችን አስቆጠረ ፤ 19 ጎል ያስቆጠረው በሴሪኤው ነው ይህም የክለብ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እንዲሆን አርጎታል ፤ በዚው ጁቬንቱስ የሴሪኤ ዋንጫ ሲያነሳ የአርጀንቲናዊው ኮከብ ዲባላ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ።
እ.አ.አ በ2016 ፖል ፖግባ ለማንቸስተር ዩናይትድ መፈረሙን ተከትሎ ክለብ ጁቬንቱስ ለዲባላ የ10 ቁጥር ማሊያን እንዲለብስ ቢያቀርብለትም ዲባላ ውድቅ በማድረግ ቀድሞውን የሚለብሰው 21 ቁጥር ማሊያን መልበስ ምርጫው አድርጓል ፤ በመቀጠል የጁቬው አሰልጣኝ ማስሚላኖ አሌግሪ በ4-2-3-1 አስተላለፍ መጠቀም መጀመራቸውን ተከትሎ ዲባላ ከጎንዛሎ ሂጉዌን ጀርባ በመሰለፍ መጫወት ጀመረ ፤ ይህም ዲባላ እንደቀድሞ ጎል እንዲያስቆጥር ምክንያት ሆነ። በይበልጥ መከላከል እና የጎል ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ ጨመረ ፤ ከዛም በኋላ በቻምፒየንስ ሊጉ ጁቬንቱስ ዳይናሞ ዛግሬብን 4-0 ሲያሸንፉ ዲባላ በጨዋታው ጎል አስቆጠረ ፤ ከቀናት በኋላ በሴሪኤው ኢምፖሊን ሲያሸንፉ ዲባላ ጎል አስቆጥሯል ።
በሚያዚያ 11,2016 በቻምፒየንስ ሊጉ ሩብ ፍፃሜ ጁቬንቱስ ባርሴሎናን 3-0 ሲረታ አርጀንቲናዊው ኮከብ ዲባላ በጨዋታው ላይ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ክለብን ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲሻገር አግዟል ፤ የዲባላን ብስለት ፣ የአጨራረስ ሁኔታ ፣ በሜዳ ላይ በሚያሳያቸው ማራኪ እንቅስቃሴዎች የተመለኩቱት የጁቬንትስ ሀላፊዎችን ለተጫዋቹ ውሉን እንዲያራዝም ጥያቄ አቀረቡለት ፤ በሚያዚያ 13 2017, ዲባላ በቱሪን እስከ 2022 ድረስ የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ፈረመ ፤ በሰኔ 3,2017 በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጁቬንቱስ ከስፔኑ ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድ ተገናኙ ፤ በዚህ ጨዋታ ላይ ዲባላ ቋሚ 11 ውስጥ በመግባት ጨዋታውን ጀመረ ፤ ነገርግን ሪያል ማድሪድ ጁቬንቱስን 4-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የቻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫን አሳኩ ፤ የጁቬ የሶስትዮሽ ዋንጫ የማሳካት ዕድላቸው አመለጣቸው ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉዳት ማስተናገድ የጀመረው ዲባላ ቀስ በቀስ የተጠበቀውን ያክል መንቀሳቀስ ሳይችል ቀረ። ሆኖም ግን በርካታ ክለቦች እሱን ለማስፈረም ሙከራን ቢያረጉም እሱ ግን ሌላኛውን የጣሊያን ክለብ ሮማን ምርጫው በማድረግ ከ2022 አንስቶ በሮማ ቤት እየተጫወተ ይገኛል ። እኛም የመልከ መልካሙን እና አይነ ግቡን አርጀንቲናዊ ኮከብ ፓውሎ ዲባላን የህይወት ታሪክ የዳሰስንበት ፕሮግራማችን ይህን ይመስል ነበር በቀጣይ በሌሎች ፕሮግራሞች እስክንገናኝ ሰላም !