ታላቁ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በቀያይ ሰይጣኖች ቤት ትልቅ ክብር የሚሰጠውን ሰባት ቁጥር ለአንድ ፖርቹጋላዊ ታዳጊ እንዲለብስ ሲሰጡት በብዙዎች ዘንድ ግርምትን የፈጠረ አጋጣሚ ነበር። ምን ያህል ልጁ ቢያሳምነው ነው ኤሪክ ካንቶና ፤ ዴቪድ ቤክሀም ፤ ጂዮርጅ ቤስት ያጠለቁትን ቁጥር የሰጠው? የአብዛኞቹ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ጥያቄ ነበር። በክለቡ ባሳለፈው የስደስት አመት ቆይታዉ ግን የተጠራጠሩትን ብቻ ሳይሆን የሚያቁትን ጭምር አምኖ ለመቀበል ሚያቅቱ ትርኢቶቹን አስመልክቷል። ከየትኛውም የሜዳ ክፍል የሚሰዳቸው ኳሶች ልክ እንደ ማግኔት ማረፊያቸው ተመሳሳይ ቦታ ነው ሚያርፈው ጎል ና ጎል ብቻ። ኳስ ይዞ ሲገሰግስ ተከላካዮች ለማቆም ሳይሆን ለመግጠም የሚፈሩት አውሬ ፤ አሸናፊነት ና ተስፋ አለመቁረጥን በመድሀኒት መልክ የወሰደ እስኪመስል ታላቅነቱን በገሀድ አስመሰከረ። ቀጣዩ መዳረሻውን ስፔን አድርጎ እግሩን ከሳንቲያጎ ቤርናቦ አሳረፈ። ሪያል ማድሪድን ወደ አውሮፓ ንግስናቸው ለመመለስ ባየር ሙኒክን በቀዝቃዛዉ ምሽት በገዛ ደጋፊዎቻቸው ፊት አፌዞባቸዋል ፤ የአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች ለ100 አመታት የሚያወሩትን መጥፎ ጠባሳ ጥሎባቸዋል ፤ ጁቬንቱሶች 7 ቁጥር እንዲፈሩ አድርጓቸዋል ፤ የጓርዲዮላዉ ባርሴሎና እንዲበታትን ትልቁን አሻራ አስቀምጧል ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለው እምነት የጣሉበትን የማድሪድ ደጋፊዎችን ፈገግታ በየእለቱ ለመመልከት ብቻ ነበር። የቻምፕዬንስ ሊግ ምሽቶች በደረሱ ቁጥር የመፅኼቶች ቁንጮ ፤ የጋዜጦች ሂስ ፤ የመረጃዎች ርዕስ የሚሆነው ስም ያለ-ማቅማማት “ክርስቲያኖ ሮናልዶ” ሆነ።
ሌሎች አንዴ አሳክተው መገለጫቸው የሚያደርጓቸውን ታላላቅ ሽልማቶች ክርስትያኖ ደጋግሞ ተጎናፅፏል ፤ ለሌሎች መገለጫ ቢሆኑም ለሱ ከማጌጫ ያለፉ ትርጉም አልነበራቸውም በእሱ አስተሳሰብ ሁሌም ነገ አለ! ቡፎን ፤ ኦብላክ ፤ ዴሂያ ፤ ኮርቷ ፤ ኑየር ፤ ቫልዴስ ፤ ቼክ እና የመሳሰሉ ታላላቅ በረኞች በእግሩ አርጩሜ ክፉኛ ከቆሰሉ ግለሰቦች ዋነኞቹ ናቸው። ሚሊዬኖች የሱን ስኬቶች ወደላይ እየተመለከቱ ተስፋ ይሰንቃሉ ፤ አያሌ ታዳጊ እግር-ኳስ ተጫዋቾች ፈለጉን ለመከተል ይፈልጋሉ ምክንያቱም “ክርስትያኖ ሮናልዶ” አንድ ተራ የግለሰብ ስም ሳይሆን ፅናት ና ስኬት የሚቀዱበት ትልቅ ቃል ነው የትክክለኛ መንገድ አመላካች ቀለም ነው የአሸናፊነት ፎርሙላ ነው። በሌላ በኩል ያለ ሀጢያቱ ስድቦች የተቸነፈሩበት የቡድን አጋሮቹ ሳይቀር በከፍታው የሚቀኑበት ለበጎ ተግባሩ በምላሹ የተሳለቀበት ከእግር ኳስ አለም የይቅርታ ደብዳቤ የሚገባው ሆደ-ሰፊ የእግር ኳስ ቅፅል ነው። የክርስትያኖ ሮናልዶ የአውሮፓ ቆይታ በየትኛውም ጤነኛ የእግዜር ፍጥረት የማይደገም እስከ ምድር ፍፃሜ ትውልድ ሲመኘዉ የሚኖረው ተረት-ተረት ሆኖ ተስሏል። ሊዝበን ,ማንችስተር , ማድሪድ ,ቱሪን የነበረውን የንግስና አመታቱን ቋጭቶ ከአውሮፓ ውድድሮች ፈቀቅ ቢልም የእሱ የሜዳ ላይ ተግባር መቼም በማንም አይደገምም።
የሳውዲ የእግርኳስ አብዮት የቀየረ ፣ ብዙ ሚዲያዎች ሳውዲ ሊግ ለማስተላለፍ እንዲጣደፉ ያደረገ ፣ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ብዙ ኮኮብ ተጨዋቾች ወደ ሳውዲ እንዲጎርፉ መንገዱን የጠረገ ፣ ማንም አይቶት የማያውቅ እነማን ክለቦች እዛ እንደሚጫወቱ እንኳን የማያውቅ የነበረውን የዓለም የእግርኳስ አፍቃሪ አሁን እያንዳንዱ ጨዋታ እንዲከታተለው አደረገ ፣ ከታናናሽ እስከ ታላላቅ ሚዲያዎች ስለዚህ ሊግ መዘገብ ጀመሩ ፣ የሳውዲ የእግርኳስ አብዮት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ገፅታም ጭምር በዚህ የእግርኳስ ኮኮብ የበለጠ ደመቀ። ማንቸስተር ዩናይትድ ብዙ ዋንጫዎችን ወደ ኦልትራፎርድ ያመጣላቸው ከቀድሞ ኮኮባቸው ክርስትያኖ ሮናልዶ ያደረጉት ፍቺ ተቀባይነት ያልነበረው ነው። እሱ ግን ሁሌ ሌላ ድል የሚናፍቅ በፍፁም ባለው ሀብት ፣ ባለው ስኬት ፣ ባለው ምቾት እና ሽልማቶች የማይዘናጋ ሁሌ ለሌላ የስኬት ማማ የሚተጋ የአለም የእግርኳስ ኮኮብ ተጨዋች ነው። በእያንዳንዱ ጨዋታዎች ጎል ለማስቆጠር የሚያደርገው ጥረት ስታይ 900 ጎሎች ያስቆጠረ አይመስልህም ፣ በእያንዳንዱ ጨዋታ ክለቡ እንዲያሸንፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ስትመለከት ከ30 በላይ ዋንጫዎች የወሰደ ተጨዋች ነው ብለህ ለመገመት ትቸገራለህ፣ ጎል አስቆጥሮ ደስታው የሚገልፅበት መንገድ የመጀመሪያ ጎሉ ያስቆጠረ ይመስላል ፣ ጨዋታ አሸንፎ የሚደሰተው ደስታ ስታስተወል ከ700 በላይ ጨዋታዎች ያሸነፈ አይመስልም። ለስኬት ፣ ለማሸነፍ ሁሌ እንደ አዲስ የሚፋለም ድንቅ ፍጥረት ነው።
ሮናልዶ በየትም ሊግ ይሂድ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ በግልፅ የሚታይ ነው። በፕሪሚየር ሊግ ፣ በላሊጋ እና ሴሪኤ ጣልያን የመሰሉ የአለማችን ታላላቅ ሊጎች ታላቅነቱ ያስመሰከረ ተጨዋች ነው። በሁሉም ሊጎች ኮኮብ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችለዋል ፣በሁሉም ሊጎች የአመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተሸልመዋል ፣ በሁሉም ሊጎች ሀትሪኮች ሰርተዋል ፣ በሁሉም ሊጎች ዋንጫዎች ጠራርጎ ወስደዋል። በሳውዲም ቢሆን ገና በአንደኛው አመቱ ብዙ ሪከርዶች ሰባብሯል። በዚህ የውድድር ዘመን የሳውዲ ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እና ከፍተኛ ለጎል የሚሆኑ ኳሶች ያቀበለ ተጨዋች ነው። አንድ የእግርኳስ አፍቃሪ ለሮናልዶ እንዲህ ሲል ይገልፀዋል “እንደ ወይን እያደረ ይጣፍጣል ብለን ምስክርነታችንን እንዳንሰጥ ጣዕሙ ከወይን የሚበልጥ ነው፤ የኮኮቦች ኮኮብ እንዳንለው ኮኮቦች በፀሐይ የሚሸነፉ ሆኑብን ፣ የሁሉም እንስሳት ንጉስ በሆነው አንበሳ እንዳንጠራው ማሳነስ ይሆንብናል በቃ ያለውን ላለማሳነስ ስንል እናቱ በምትጠራው ክርስትያኖ ሮናልዶ በሚል ስም እንጥራው። አልናስር ከ6 አመታት በኋላ አል ኢትሀድን ሲያሸንፉ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከ30 አመቱ በኋላ 503 የጎል ተሳትፎ አድርሷል። አስቡት እስኪ ከ400 በላይ ጎሎች አይደለም ከ30 አመት በኋላ በህይወት ዘመን ለመድረስ ራሱ የሚከብድ ነው” ሲል ይደመጣል። ብዙዎች ሳውዲ ሊግ ቀላል ነው ይላሉ ቀላል ቢሆን ቤንዜማ እንዴት ብዙ ጎሎች አያስቆጥርም? ፌርሚንሆ እና ሌሎችስ? በዚህ እድሜ ይሄንን ማድረግ እጅግ ከባድ ነው። ማንምም አላደረገውም። ከአለም ዋንጫ ውጪ ሁሉም የስኬት ማማ ያጣጣመ ክርስትያኖ ሮናልዶ ዶ ሳንቶስ አቬሮ ዓለም ነው።
ጎል አግቢነት ፣ ጠንክሮ መስራት ፣ ሜዳ ውስጥ መታተር… እነዚህን የጠቀስኳቸውን ነገሮችን ማሟላት የሚችል ኳሰኛ ክርስትያኖ ሮናልዶን መተካት ይችላል!? አብዛኛው እግር ኳስ ተመልካች ሚሰጠው የሞኝ ምላሽ ነው። አው በእርግጥ ሁሌ ስኬት የተጠማ ተጫዋች ይመጣ ይሆናል.. ነገር ግን 900 ጎሎችን አግብቶ ማይዝል እግር አይኖረውም!.. እሺ ጠንካራ ና ታታሪ ተጫዋች ይኖር ይሆናል.. ሆኖም ትላንት ያገኘውን ተቆጥሮ ማያልቅ ስኬቱን ዘንግቶ : ዛሬም ስራውን አሐዱ ብሎ የሚጀምር ትሁት ፈፅሞ አይፈጠርም። ዛሬም በታላቁ ቢዝነስ ውስጥ ስሙን ማስጠራት መቻሉ ቀላል ስኬት አይደለም። ሳኡዲ መሆኑ አይደለም : የሊጉ ጥራት ማሻቀብም አይደለም : በቃ እርሱ ልዩ ስለሆነ ነው! አንድ ሺ ትችቶችን ጫንቃው ችሎ ዛሬም መፍካቱ ነው ፤ የእግር ኳስ ተጫዋች ዕድሜ ገደብን ጥሶ ማለፉ ነው : ልፋቱ ነው ፣ ጥረቱ ነው ፣ በራስ መተማመኑ ነው : እጅግ በጣም ልዩ ክስተት መሆኑ ነው። 50 ሎሚ ተሸክሞ ለ51ኛው እጁን ሚዘረጋ የሰው ተረት ተረት ማይገድበው ቆንጅዬው ጭራቅ።