ሳዲዮ ማኔ በApril 10 1992 በሴኔጋል በሴዲህዩ ከተማ ውስጥ በምትገኝ 24ሺ ህዝቦች ብቻ በሚኖሩባት ባምባሊ ተብላ በምትጠራ ቲንሽዬ መንደር ውስጥ ተወለደ ። ከ1992 ከማኔ ውልደት ቡሃላ ህይወት የተመቻች ሊሆንላቸው ያልቻሉት የማኔ ቤተሰቦች ሳዲዮ ማኔ ለትምህርት በደረሰ ጊዜ የሚከፍሉት ብር ስላልነበራቸው ትምህርት ሳያስመዘግቡት ቀሩ ። ማኔ ትምህርት መማር አለመቻሉን ተከትሎም ጊዜ ማሳለፊያ እግር ኳስን በመንገድ ላይ ከሰዎች እና ከጓደኞቹ ጋር መጫወት ጀመረ ። ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቦቹ ካለባቸው ችግር አንፃር ወጪ ለመቀነስ ሲባል ማኔን እዛው መንደር የሚኖረው አጎቱ ኢብራሂም ጋር እንዲኖር ለአጎቱ ሰጡት ። ማኔ ይናገራል ”አስታውሳለሁ 7 አመቴ ላይ እያለው ነበር እዛው በመንደራችን እንደተለመደው ኳስ በመጫወት ላይ እያለው ወንድሜ መጣ ፤ ከዛም ማኔ ”አባታችን እኮ ሞተ” ሲል ነገረኝ ። በወቅቱ ማመን ከብዶኝ እየቀለደ ነበር የመሰለኝ ፤ አባታችን የሆድ ህመም ነበረበት በኛ መንደር ደግሞ ሆስፒታል የለም ፤ ሆስፒታል ባለመኖሩ የተነሳም አባቴ ለሳምንታት እቤት ውስጥ ነበር ህመሙን ተቋቁሞ ያሳለፈው ፤ ከዛም ያ ህመሙ ጠንቶበት መሞቱ ተነገረኝ ። የመስጊድ አሰጋጅ ኢማም የነበረው የማኔ አባት ከመሞቱ አስቀድሞ በተደጋጋሚ በማኔ ምን ያህል ይኮራ እንደነበር የነገረው ትዝ ብሎት ማኔ አንድ ነገር ለራሱ ቃል ገባ ። ”አሁን እናቴን ለመርዳት የተቻለኝን ነገር ሁሉ ማድረግ አለብኝ” ሲል ለራሱ ቃል ገባ ።
ከአጎቱ ጋር መኖሩን ቀጠለ ፤ ማኔ ከኳስ መጫወት ባሻገር ጎን ለጎን ግብርናም ከአጎቱ ጋር መስራት ጀመረ ። ወደ ኳሱ ያመዘነ ፍላጎት ቢኖረውም ቀሪ ቤተሰቦቹ ሃይማኖተኛ መሆናቸውን ተከትሎ ወደ ሃይማኖቱ እንዲያተኩር ይነግሩት ጀመር ። ማኔ ግን በየቀኑ ከአጎቱ ጋር ወደ ግብርናው ሲሄድ ”እኔ ገበሬ አልሆንም እልቁንስ እኔ ኢንተርናሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ነው የምሆነው” ሲል በተደጋጋሚ ይነግረው ጀመር ።ከአጎቱ ጋር ኑሮውን ያደረገው ማኔ ከልጅነቱም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ወዳጅ ሆኖ አደገ ። ማኔ እግር ኳስን በመንገድ ላይ ከመጫወት ባለፈ ፕሪምየር ሊጉን እና የሀገራት ውድድርን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መመልከት ጀመረ ። 2002 የአለም ዋንጫ…..10ኛ አመቱ ላይ የነበረው ሳዲዮ ማኔ የህይወቱ ትልቅ ለውጥ የጀመረው በዚ የአለም ዋንጫ ነበር ። ሀገሩ ሴኔጋል አስደናቂ አቋምን ባሳየችበት የኮሪያ እና የጃፓን አለም ዋንጫ ሀገሩ ሴኔጋል የወቅቱ የአለም ሻምፒዮናዋን ፈረንሳይን በመክፈቻ ጨዋታ ማሸነፍ ቻለች ።
ፈረንሳይን በማሸነፍ ውድድሩን የጀመረችው ሴኔጋል በአስደናቂ ሁኔታ በአለም ዋንጫው እስከ 8 ውስጥ መጓዝ ቻለች ። በወቅቱ መነጋገሪያ የነበረችው ሴኔጋል ለነ ሳዲዮም የእግር ኳስ ህይወት መነሳሻ መሆን ቻለች ። ሳዲዮ ማኔ ሲናገር የሀገራችንን የሴኔጋልን አቋም ከተመለከትን ቡሃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንደራችን የወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር አዘጋጀን ፤ ከዛም በውድድሩ ላይ የተመለከተኝ ሁሉ የዚ መንደር ምርጡ ተጫዋች አንተ ነህ ይለኝ ጀመር ። በእኔ የእግር ኳስ ህይወት አጎቴ በከፍተኛ ደረጃ ይረዳኝ ጀመር ፤ ከአጎቴ በተጨማሪም የመንደሩ ሰው ሳይቀር በየጨዋታው ብር እያዋጣ ይሰጠኝ ጀመር ። ቤተሰቦቼም ከኳስ ሌላ ምንም ፍላጎት እንደሌለኝ ሲያውቁ ሃሳቤን መቀበል ጀመሩ ፤ በኔ ቤተሰብ ዘንድ ኳስ መጫወት ማለት ጊዜን መግደል ማለት ብቻ ተደርጎ ነው የሚታሰበው….ሌላ አንድም ትርፍ በኳስ እንደማይገኝ ነበር የሚታሰበው ።15ተኛ አመቴ ላይ ወደ ሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ለልምምድ ልሄድ ስል አጎቴ እና ቤተሰቦቼ ከግብርና ምርት የሰበሰቡት እህሎች በመሸጥ የተገኘውን ገንዘብ አሰባስበው ሰጡኝ ። ጉዞ ወደ ዳካር….ማኔ ሲናገር ዳካር ካቀናሁ ቡሃላ በከተማው አንድም የማውቀው ሰው አልነበረም ፤ አንድ ቤተሰቤን የሚያውቃቸው ሰው ግን ምንም የማላውቃቸው እሱ የሚያውቃቸው አንድ ቤተሰብ ጋር ወሶዶ እንዲያኖሩኝ አስተዋወቀኝ ፤ ከዛም ለነሱ የተወሰነ ብር ሰጠኋቸው ፤ ከሰጠኋቸውም ቡሃላ ስለ ሁኔታው አስረዳኋቸው ። እነሱም ካዳመጡኝ ቡሃላ እንደ ቤተሰብ ተቀበሉኝ እነሱ ጋርም መኖር ጀመርኩ ። ከተወሰነ ጊዜ ቡሃላ በዳካር የሚገኝ ትልቅ ክለብ ለምልመላ ሄድኩ እንደ ሄድኩኝ ብዙ ወጣት ተጫዋቾች በቦታው ተገኝተው ነበር ፤ ከዛም መልማዩ አጠገቤ መጥቶ ”እዚ ለፈተና ምልመላ ነው የመጣከው ?” ሲል ጠየቀኝ ”አዎ” ብዬ መለስኩለት ። ከዛም በዚ ጫማ ? ሲል በግርምት መለሰልኝ ። ጫማዬ የተቀደደ እና የወላለቀ ነበር ፤ ቀጠለና በዚ ቁምጣ ? ለእግር ኳስ የሚሆን ትጥቅ እንኳን የለህም ? ሲልም ጠየቀኝ
መጫወት ብቻ እንደምፈልግ ነገርኩት ከዛም ተጫወትኩ በሜዳም ላይ ጥሩ አቋምን አሳየው ከዛም ከተመረጡት ውስጥ አንዱ መሆን ቻልኩኝ ። በዛ የዳካር ዝነኛ ክለብ በ90 ጨዋታዎች 131 ጎሎችን አስቆጠርኩ ። ከዛም ከጊዜያቶች ቡሃላ የህይወቴ ትልቁ እድል መጣልኝ.. የፈረንሳይ መልማዮት ወደ ዳካር መጡ ፤ ዳካር የመጡት በጣም ደሃ የሆኑ ወጣት ተፈጥሮአዊ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾችን ለመመልመል ነበር ። እንደ እድል ከተመረጡት ተጫዋቾች አንዱ መሆን ቻልኩኝ ። መልማዮቹ ወደ ፈረንሳይ ወሰዱኝ Metz ክለብን ተቀላቀልኩኝ ፤ ወደ ፈረንሳይ ስሄድ ለአጎቴ ብቻ ነው የነገርኩት እናቴ እና ቀሪ ቤተሰቦቼ ሰርፕራይዝ ላደርጋቸው ስል ስሄድ አልነገርኳቸውም ነበር ። አስታውሳለሁ የመጀመሪያ ቀን ወደ ፈረንሳይ ስሄድ ፤ ልምምድ ነበረብኝ ነገር ግን አሰልጣኛችን ቤትህ ቆይ አለኝ ። ያን ቀን ወደ እናቴ ስልክ መደወል ፈልጌ ነበር ነገር ግን ስልክ ለመደወል በቂ የሞባይል ካርድ አልነበረኝም ። በቀጣዩ ቀን ሜትዝ የሚጫወቱ ጓደኞቼ ጋር ሄጄ ካርድ ገዛሁ ፤ ለእናቴም ደወልኩላት እና “ፈረንሳይ ደርሻለሁ” አልኳት ። እናቴም ”የትኛዋ ፈረንሳይ ?’ ስትል መለሰችልኝ እኔም አውሮፓ የምትገኘዋ ፈረንሳይ ነኝ ስል ነገርኳት ፤ ልታምነኝ አልቻለችም ፤ ቀጠለችና የትኛዋ አውሮፓ ? አንተማ ሴኔጋል ነህ አለችኝ ።ከዛም ቀን ቡሃላ በየቀኑ በደወለች ቁጥር የነገርከኝ ነገር ግን እውነት ነው ? ስትል ደጋግማ ትጠይቀኝ ነበር ይላል ሳዲዮ ማኔ በመጨረሻም ኳስ ባለኝ ቀን ቴሌቭዥን ከፍተሽ ይሄንን ጨዋታ ተመልከቺ ብዬ ነገርኳት ከዛም ለmetz ስጫወት አየችኝ እንዳልዋሸኋትም ተረዳች ።
ከዛም ማኔ በመትዝ ተጫውቶ ወደ ሳልዝበርግ ከሳልዝበርግ ድንቅ አቋም ቡሃላ ሳውዝሃምፕተን ከዛም ከአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች አንዱ ወደ ሆነው ሊቨርፑል ማቅናት ቻለ ። ማኔ በሊቨርፑል የአለማችን የክለቦች ትልቁን ዋንጫ ቻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ ፕሪምየር ሊጉ ፣ EFL CUP ፣ FA CUP ፣ የአለም ክለቦች ዋንጫን እና ሱፐር ካፕን ማሸነፍ ቻለ ። በብዙ ልፋቶች ትልቅን ደረጃ የደረሰው ሳዲዮ ማኔ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ ቡሃላ በ2019 በትውልድ ከተማው ትልቅ ትምህርት ቤትን ገነባ ። አባቱ ሊያገኘው ያልቻለውን የህክምና ህስፒታልንም ለመንደሩ ነዋሪዎች በ40 ሚልየን ብር (684 ሺ ዶላር) አስገነባ ። ለአጎቱ እና ለእናቱ ለቤተሰቦቹ ቤት እና መኪና በተጨማሪም የተሻለ ህይወትን እንዲኖሩ ማድረግ ቻለ ። ማኔ ከቤተሰቡ አልፎም በትውልድ ከተማው ለሚገኙ ለ2ሺ ያህል ነዋሪዎች በየወሩ 70 ዶላር (3500 ብር) ደሞዝ መስጠትም ጀመረ ። ማኔ 500ሺ ዶላር ለሴኔጋል መንግስት ኮሮናን ለመከላከል በሚል ከመስጠት ጀምሮ በብዙ በጎ አድራጎቶችም ላይ መሳተፍ ጀመረ ። በችግር ምክንያት አጎቱ ጋር ያደገው ማኔ እንዲህ ሲል ይናገራል ”በራሳችሁ ልታምኑ ይገባል ሁሌም ቢሆን በምታደርጉትም ነገር ልታምኑ ይገባል”