አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌና ፌዴሬሽኑ በጊዜ ተለያይተዋል
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ብ/ቡድኑን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተወስናል
በእርግጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ያላቸው የአንድ አመት የኮንትራት ስምምነት የሚጠናቀቀው ከስምንት ቀን በኃላ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ነው፤የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሠባ ላይ ከአሠልጣኙ ጋር የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው የሚጠቁም ውሳኔ ኮንትራቱ ቀሪ ስምንት ቀን እያለው ቀድሞ አሳልፏል።
ሀትሪክ ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባገኘችው ታማኝ መረጃ መሠረት ብ/ቡድኑን በምክትል አሠልጣኝነት ሲያገለግል የነቀረውን አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ በዋና አሠልጣኝነት እንዲመራ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
በቀጣይ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን የማጣሪያ ውድድር ይደረጋል በዚህ ውድድር ላይ ከሱራፌልና ከአቤል ማሞ በስተቀር ሁሉም የብ/ቡድን ተጫዋቾች በቻን ውድድር ላይ የሚሳተፉ በመሆኑ በምክትል አሠልጣኙ መመራት ይችላል በማለት አሠልጣኝ መሳይ ተፊሪ በጊዜያዊነት እንዲሾም ስራ አስፈፃሚው መወሠኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ማጣርያ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችን በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት እየተመራ እንዲያከናውን የኢ/እ/ፌ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ አሳልፏል።
ይህ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ያላቸው የኮንትራት ስምምነት ከመጠናቀቁ ስምንት ቀን ቀድሞ የተላለፈ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች አሠልጣኞችን ተረጋግቶ ለማየት ዕድል ይሠጣል እስከዛ በጊዜያዊነት ምክትሉ ሸፍኖ ይስራ የሚል ውሳኔ ላይ መደረሱን ሀትሪክ ከታማኝ ምንጮቿ ተረድታለች።
በፌዴሬሽኑ አዲስ ኃላፊነት የተሠጠው አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ረዳት በመሆን ላለፉት 12 ወራት ያገለገለ ሲሆን በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኤርትራ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ጨምሮ ሌሎች ማጣሪያዎችንም በእሱ ዋና አሠልጣኝነት በጊዜያዊነት መሾሙን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።